=<({አል-ኢኽላስ 112:1-4})>=
ﺑﺴﻢ ﺍﻟﻠﻪ ﺍﻟﺮﺣﻤﻦ ﺍﻟﺮﺣﻴﻢ
1. በል! እርሱ አላህ አንድ ነው።
2. አላህ (የሁሉ) መጠጊያ ነው።
3. አልወለደም፤ አልተወለደምም።
4. ለእርሱም አንድም ብጤ የለውም።
![]() =<({አል-ቁርአን 96:1-5})>=
![]() በቡኻሪ በተዘገበው ሐዲስ መሰረት እውቀትን መሻት በእያንዳንዱ ሙስሊም ላይ ግዴታ ነው። ![]() |
---|
ምስጋና ለአለማት ጌታ ለሆነው ለአሏህ ይገባው። የአሏህ ሰላምና እዝነት በረሱል(ሰ.ዐ.ወ)ና በቤተሰቦቻቸው እንዲሁም የሳቸውን ፈለግ በተከተለ ላይ ሁሉ ይሁን።
የሰው ልጅ ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ ማለትም አደም አለይሂ ሰላም ወደዚች አለም ሲመጣ ከአሏህ ዘንድ የነገራቶችን ስምና እውቀት አሏህ ችሮት ነው። ከዚህም አልፎ ለነብዩ ሙሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) የመጨረሻው ወህይ (ቁርአን) ሲገለፅላቸው የመጀመሪያው ቃል «ኢቅራ» አንብብ የሚል ነበር። ይህ ምን ያህል እውቀት በኢስላም ቦታ ያለው መሆኑን የሚያመላክት ነው።
=<({አል-ቁርአን 58:11})>=
«አሏህ ከእናንተ መካከል እነዚያ ያመኑትንና እውቀት የተቸሩትን በደረጃ ከፍ ያደርጋል።»
እንዲሁም በቡኋሪ በተዘገበው ሐዲስ መሠረት እውቀትን መሻት በእያንዳንዱ ሙስሊም ላይ ግዴታ ነው።
ኢማሙ ሙሐመድ አልገዛሊ እንዳሉት እውቀት የእያንዳንዱ ተግባር ፣ የስራ ወይም የእምነት መሰረት ነው። ካለ እውቀት መልካምነትና ደግነት በዚህም ሆነ በመጭው አለም ሊገኝ አይችልም። ስለዚህ እንደተባለው ከእውቀት በላይ ወደ አሏህ የሚያደርስ (የሚያመራ) መንገድ የለም በእውቀት ቢሆን እንጂ። የሰው ልጅ ጌታውን በብቸኝነት እንዳይገዛ ከሚያደርጉት ነገሮች መካከል አንዱ የሰው ልጅ ልብ በድንቁርና ፅልመት መሸፈኑ ነው።
እውቀት የህይወት መሠረት ነው። በእውነቱ እውቀት በራሱ ህይወት ነው። እንዲሁም ድንቁርና የሞት መሠረት ሲሆን ድንቁርና በራሱ ደግሞ ሞት ነው።
ከእውቀት ባሻገር ከሁሉም ነገር በላይ ከአሏህ ዘንድ የተወደደ ነገር ቢኖር ኖሮ ለአደም(ዐ.ሰ) ይሰጠው ነበር። አሏህ በቁርአኑ እንዲህ ይላል፦
=<({አል-ቁርአን 3:18})>=
{18} «አሏህ በማስተካከል የቆመ አስተናባሪ ሲሆን ከእሱ በቀር ሌላ አምላክ የሌለ መሆኑን መሠከረ። መላዕክቶችና የእውቀት ባለቤቶችም እንዲሁ መሠከሩ። ከእርሱ በቀር ሌላ አምላክ የለም። አሏህ አሸናፊና ጥበበኛ ነው።»
ከዚህ መገንዘብ እንደሚቻለው አሏህ(ሱ.ወ.ተ) ራሱን በመጥቀስ ይጀምርና በሁለተኛ ደረጃ መላዕክቶችን ያወሳል። ከዚያም በሶስተኛ ደረጃ የእውቀት ባለቤቶች ሲል ይጠቅሳል።
በሌላ አያ ደግሞ አሏህ የራሱን እና የኡለማዎች ምስክርነት በቂ እንደሆነ ያመላክታል።
=<({አል-ቁርአን 13:43})>=
«በእኔና በእናንተ መካከል መስካሪ በአሏህና እርሱ ዘንድ የመፅሐፉ እውቀት ባላቸው በቃ በላቸው።»
በሌላ የቁርአን አያህ አሏህ እንዲህ ይላል:-
«በእርግጥ አሏህን ፈሪ አገልጋዮች ሊቃውንቶች ናቸው።»
ለዚህ ምክኒያቱ ግልፅ ነው። በእርግጥ አንድ ሰው ካለ እውቀት የአሏህ ፍራቻ ሊኖረው አይችልም። እንዲሁም የአሏህን ቁጣ ፣ የጀሃነምን ቅጣት ፣ የቂያማን መከራ ካለ እውቀት ሊረዳ የሚችል የለምና ነው።
ረሱል(ሰ.ዐ.ወ) «አሏህ ከሁሉ በላይ ቸር ነው። እኔ ከእናንተ መካከል በጣም ለጋስ ነኝ እናም ከእኔ ብኋላ ከእናንተ መካከል በጣም ለጋስ የሆነው እውቀትን የሚሽትና የሚያስፋፋት ነው» ብለዋል።
ኢማሙ ዘሃቢይ እንደዘገበው ረሱል(ሰ.ዐ.ወ) «በፍርዱ ቀን የኡለማዎች (የሊቃውንት) የቀለም ማሰሮ እና የሰማእታት ደም ወደ ፊት ይመጣል። የኡለማዎች ቀለም ከሰማእታት ደም በላይ ይሆናል» ብለዋል።
በሐዲስ ሸሪፍ እንደተዘገበው አንድ ሰው እውቀትን በመሻት ላይ እያለ የሞተ አሏህን በዚያው ሁኔታ ላይ ይገናኛል።
በሙአሊመቱ ተንዚል እንደተዘገበው ረሱል(ሰ.ዐ.ወ) «አንድ ሰው እውቀትን ለመሻት ሲጔዝ መላኢካዎች ክንፎቻቸውን ከእግሩ ስር ያደርጉለታል ፤ ሰማያትና ምድር እንዲሁም የውቅያኖስ አሳዎች ዱአ ያደርጉለታል።» ብለዋል።
የእውቀትን ታላቅነት ለመረዳት እውቀት ከአሏህ ባህሪያት መካከል አንዱ መሆኑን መገንዘብ በራሱ በቂ ነው። በዚህም ሆነ በመጭው አለም የህይወታችን መድህን የብልፅግናችን መሠረቱ እውቀት ነው። እውነታውን ስንመለከት እውቀት የሌለው ሰው እንሰሳ ነው። የሰው ልጅ ልዩና ታላቅ የሚያደርገው ነገር እውቀቱና ንግግሩ ነው። ይህ ለኛ ጠቃሚ ከሆነ የእውቀትን ሃብት ለማግኘት ሁሌም መጣር ይጠበቅብናል።
እውቀትን በመሻት መንገድ ላይ ሆነን የሚገጥሙን መሰናክሎች የሚከተሉት ናቸው፦
ከተረገመው ሸይጧን ዘንድ በጣም የተጠላና በጣም አደገኛ ነገር ቢኖር እውቀትን መሻት ነው። ይህን ጣልቃ ገብነት ፣ መሰናክል ለመዋጋት በጣም ቀላሉ ዘዴ የቁርአን አያቶችን እና ሐዲሶችን ማስታዎስ ሲሆን እንዲሁም ለሸይጧንም ጉትጎታና ማዘናጊያ ትኩረት አለመስጠት ነው።
መከራን ስትጠላ መዝናናትን እና መንፈስን ማርካታ ትወዳለች። በእርግጥ አንድ ሰው የዱንያን ጊዜያዊነትና የአሂራን ዘላለማዊ መኖሪያነት ሲረዳ እውቀትን የመሻት መከራ ለአጭር ጊዜ የሚቆይ ይሆንና ደስታውና ጥቅሞቹ እልቆቢስ ይሆኑለታል።
የዚህ ብልጭልጭ አለም ሃብት ጠፊና ከእውቀት ጋር ሊነፃፀር የማይችል ነው። አንድ ሰው ሲሞት ሃብቱ አይከተለውም ይልቁንስ ወደ መቃብሩ የሚከተለውና ጀነት እስኪገባ ድረስ የሚረዳው ነገር ቢኖር እውቀት ነው።
ውድ ሙስሊም እህት ወንድሞቼ ከገባንበት የድንቁርና አሮንቃ እንውጣ። በዚች ጊዜያዊ መኖሪያ አብዛሃኛዎን ጊዜያችነን ለምን በማይረባ ፍሬ ቢስ በሆነ ነገር እናባክነዋለን። ስለዲናችን እውቀትን የምንሻበት ሰአት ይኑረን!!! በዚህም ሆነ በመጭው አለም እውቀት ጠቃሚ ነው። ከእፍረትና ከውርደት እንድናለን። ይህን ትልቅ ሃብት ለመከሰብ ጊዜያችንንና ገንዘባችነን በእውቀት ላይ ኢንቨስት እናድርግ። አዲስ ነገርን ለማውቅ ከፍተኛ ጉጉት ይኑረን።
የወጣቱ ተልዕኮ አድራሻ
ኢስላማዊ መጽሐፎችን ያውርዱ |
---|